ቻይናውያን ሳይንቲስቶች እስካሁን ከታወቁት ተክሎች ሁሉ አስቸጋሪ የአየር ንብረትና የአካባቢ ሁኔታዎችን በመቋቋም ቀዳሚ ነው የተባለ የበረሃ ተክል ለይተው አውቀዋል። ተክሉ አብዛኞቹን ተክሎች የሚገድሉ ሁኔታዎችን ማለትም ከባድ ድርቅን፣ ኃይለኛ ጨረርን፣ ጽኑ ብርድንና ከማርስ ጋር የሚመሳሰሉ የሕዋ አካባቢዎችን ተቋቁሞ መኖር ይችላል።

ተክሉ ሲንትሪኪያ ካኒነርቪስ (Syntrichia caninervis) የተባለ የሽበት ዓይነት ሲሆን ተመራማሪዎቹ በሰሜን ምዕራብ ቻይና በሚገኘው የሺንጂያንግ ዊጉር ራስ ገዝ ክልል በረሃ ውስጥ አግኝተውታል። እስካሁን ከተገኙት የበረሃ ተክሎች ሁሉ እጅግ ጠንካራው እንደሆነም ገልጸዋል።

የዚህ አስደናቂ ጥንካሬ የቅርብ ጊዜ ማረጋገጫ የተገኘው ከሕዋ ነው። ባለፈው ማርች ወር የደረቀ የሽበቱ ናሙና በቻይና የሙከራ የጭነት የሕዋ መንኮራኩር ተጭኖ በምሕዋር ዳግም ሕያው የማድረግ ሙከራ ተካሂዶበታል። በዝቅተኛ የስበት ኃይልና በሕዋ ጨረር ውስጥ ቁጥጥር የሚደረግበት የመስኖ ሥርዓት እጅግ አነስተኛ ውሃ ብቻ ቢሰጠውም ሽበቱ ሕይወቱን መልሶ ቀለሙ ከጥቁር ግራጫ ወደ ቢጫማ አረንጓዴ ተቀይሯል።

የቻይና ሳይንስ አካዳሚ አካል የሆነው የሺንጂያንግ የሥነ ምሕዳርና የጂኦግራፊ ተቋም ተመራማሪ እንደገለጹት፣ አንድ ሙሉ ተክል ወደ ዝቅተኛ የምድር ምሕዋር ተልኮ በተሳካ ሁኔታ ዳግም ሕያው ሲሆን ይህ የመጀመሪያው ነው። በምሕዋር የተደረገው ተከታታይ ክትትል ሽበቱ እድገቱን መቀጠሉን ያሳየ በመሆኑ ለጥልቅ ሕዋ የሕይወት ሳይንስ ምርምር ተመራጭ ቁስ መሆኑን አመልክተዋል።

ተመራማሪዋ በ2024 ስለዚህ ሽበት ጥናት አሳትመው ከምድር ውጭ ያሉ አካባቢዎችን ለመስፈር ፈር ቀዳጅ ተክል እንደሆነ ገልጸው ነበር። ተመራማሪዎቹ ተክሉ በሴሎቹ ውስጥ ካለው ውሃ ከ98 በመቶ በላይ ቢያጣም እንደሚቋቋም፣ በሲቀነስ 196 ዲግሪ ሴልሺየስ በፍጥነት ከቀዘቀዘ በኋላም በሕይወት እንደሚቆይና ኃይለኛ የጋማ ጨረርን እንደሚቋቋም አረጋግጠዋል።