የአሜሪካ የኅዋ ምርምር ተቋም ናሳ በማርስ ላይ የንጋትን ገጽታ የሚያሳይ ፎቶ ይፋ አድርጓል። ፎቶውን ያነሳው በቀዩ ፕላኔት ገጽ ላይ የአሰሳ ተልዕኮውን የቀጠለው ኪዩሪዮሲቲ (Curiosity) የተባለው ሮቨር ነው።
ፎቶው ከቢሊዮኖች ዓመታት በፊት የተፈጠሩ ረጃጅም የአለት ቅርጾችን የፀሐይ ጨረር ሲያበራቸው ያሳያል። ፎቶው የተነሳው ፀሐይ ከወጣች ከአንድ ሰዓት ገደማ በኋላ ሲሆን፣ ቦታው ለረጅም ዘመናት በነፋስና በአየር ንብረት ተጽዕኖ የተቀረጹ የአለት ቁልቁለቶች ያሉበት አካባቢ ነው።
በናሳ የጄት ፕሮፐልሽን ላብራቶሪ የፕላኔቶች ሳይንቲስት አሽዊን ቫሳቫዳ በአድማሱ ላይ የሚታዩት ቅርጾች ሮቨሩ እስካሁን ከመረመራቸው የተለየ የጂኦሎጂ ንብርብር አካል መሆናቸውን አስረድተዋል። እንደ እሳቸው ግምት፣ ቅርጾቹ በነፋስ ከተጓጓዙ ደለሎች ተፈጥረው በኋላ በመሸርሸር 'ያርዳንግ' በመባል የሚታወቁ ተከታታይ ኮረብታዎች ሆነዋል።
ሳይንቲስቶች ይህ ንብርብር የተፈጠረው ከሦስት ቢሊዮን ዓመታት ገደማ በፊት እንደሆነና በማርስ የጌል ጉድጓድ መሃል በሚገኘው የሻርፕ ተራራ ሰሜን ምዕራባዊ ጠርዞች ላይ 16 ኪሎ ሜትር ያህል እንደሚዘረጋ ይገምታሉ።
ኪዩሪዮሲቲ በ2012 በጌል ጉድጓድ ያረፈ ሲሆን ከ2014 ጀምሮ የሻርፕ ተራራን እየወጣ ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዟል። ናሳ ሮቨሩ በ2027 እና በ2028 ወደ 'ያርዳንግ' ንብርብር ደርሶ የጂኦሎጂ ባሕርያቱን እንደሚያጠና ይጠብቃል፤ ይህም የማርስን ታሪክና ቀደም ሲል ለጥቃቅን ሕዋሳት ሕይወት ምቹ ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን በተሻለ ለመረዳት ያግዛል።
