የሳዑዲ ዓረቢያ የሰው ሀብትና ማኅበራዊ ልማት ሚኒስትር ኢንጂነር አሕመድ ቢን ሱለይማን አል-ራጂሒ በ12ኛው የሪያድ የኢኮኖሚ ፎረም ተሳትፈው "ዕውቀትንና ልምድን በአገር ውስጥ ሠራተኞች ዘንድ የማስረጽ ስትራቴጂና በሳዑዲ ተቋማት አፈጻጸም ላይ ያለው ተጽዕኖ" በሚል ርዕስ የተካሄደውን የውይይት መድረክ መርተዋል።
ሚኒስትሩ የሁለቱ ቅዱሳን መስጊዶች አገልጋይ ንጉሥ ሳልማን ቢን ዐብዱልዐዚዝ አል-ሳዑድ ለፎረሙ ላደረጉት ድጋፍና ልዑል አልጋ ወራሽና ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ቢን ሳልማን ቢን ዐብዱልዐዚዝ አል-ሳዑድ ለግሉ ዘርፍ ለሚያደርጉት ቀጣይ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ሚኒስቴሩ ሕጎችን፣ ተነሳሽነቶችንና መርሐ ግብሮችን ባካተተ የተቀናጀ ሥርዓት የአገር ውስጥ ክህሎቶችን በማሳደግ ከሥራ ገበያው ፍላጎትና ከሳዑዲ ራዕይ 2030 ግቦች ጋር እያጣጣመ መሆኑን ገልጸዋል።
በ2023 የክህሎትና ሥልጠና ኤጀንሲ መቋቋሙን፣ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ተወካዮችን ያካተቱ 16 የዘርፍ የክህሎት ምክር ቤቶች መመሥረታቸውንና እነዚህም 13 የዘርፍ የክህሎት ማዕቀፎችን ማፍራታቸውን ጠቅሰዋል። ከ10 ሺህ በላይ ክህሎቶችንና ከ2000 በላይ ሙያዎችን የሚሸፍን የሳዑዲ የክህሎት ምደባ መመሪያም ተዘጋጅቷል።
የሙያ መመሪያና የምክር መርሐ ግብሩ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ የትምህርት ቤት ተማሪዎችንና 350 ሺህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን የገለጹ ሲሆን ከግሉ ዘርፍ ጋር የተጀመረው "ዋዕድ" የተሰኘው ብሔራዊ የሥልጠና ዘመቻ በመጀመሪያና በሁለተኛ ምዕራፎቹ ከ4 ሚሊዮን በላይ የሥልጠና ዕድሎችን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።
የሪያድ የኢኮኖሚ ፎረም ባለሙያዎችን፣ ውሳኔ ሰጪዎችንና የግሉን ዘርፍ በኢኮኖሚና በልማት ጉዳዮች ላይ ለመወያየት የሚያሰባስብ ብሔራዊ መድረክ ነው።

