የሳዑዲ ዓረቢያ የቱሪዝም ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ሰባት የኦንላይን መድረኮችን አግዷል። ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው መድረኮቹ የቱሪዝም ሕግን በመጣስ የሀገር ውስጥ የዑምራ ፓኬጆችንና የጉብኝት ጉዞዎችን ጨምሮ የጉዞና የቱሪዝም አገልግሎቶችን ሕጋዊ መስፈርቶችን ሳያሟሉ ሲሰጡ ነበር።

እርምጃው በቱሪዝም እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሕገ-ወጥ አሠራሮችን ለመቀነስ፣ የቱሪስቶችንና የዑምራ ተጓዦችን መብት ለማስጠበቅ እንዲሁም ከማጭበርበርና የጥራት መስፈርት ከማያሟሉ አገልግሎቶች ለመጠበቅ የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናስር አል-አንሳሪ ሚኒስቴሩ የኦንላይን የጉዞ መድረኮችን ጨምሮ በተለያዩ የቱሪዝም እንቅስቃሴዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥሰቶችን መከታተሉን እንደቀጠለና በጣሾች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጠዋል። የቱሪስቶችና የዑምራ ተጓዦች ደህንነት፣ መብታቸው መጠበቅና የሚሰጣቸው አገልግሎት ጥራት ምንም ዓይነት ቸልተኝነት የማይፈቀድባቸው ቅድሚያ ጉዳዮች መሆናቸውንም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሚኒስቴሩ ቱሪስቶችና የዑምራ ተጓዦች መብታቸውን ለማስጠበቅና የአገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ ፈቃድ ካላቸው መድረኮችና የጉዞና ቱሪዝም ቢሮዎች ጋር ብቻ እንዲገበያዩ ጥሪ አቅርቧል።

በሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩና የዑምራ ወይም የጉብኝት ፓኬጆችን በኦንላይን የሚገዙ ሰዎች ከመመዝገባቸው በፊት የአገልግሎት ሰጪውን ፈቃድ ማረጋገጥ እንዳለባቸው ይህ ጥሪ ያሳያል።