የሳዑዲ ዓረቢያ ጤና ሚኒስትር ፋህድ ቢን አብዱራሕማን አልጀላጅል የቀይ ባሕር ሆስፒታልን መርቀው ከፍተዋል። የሳዑዲ ዜና አገልግሎት (SPA) እንደዘገበው ሆስፒታሉን የገነባው ሬድ ሲ ኢንተርናሽናል ኩባንያ ሲሆን፣ "ሬድ ሲ ሄልዝ" በተባለው ሥርዓት ሥር በቀይ ባሕር መዳረሻ ውስጥ ይገኛል። ሥራውንና አስተዳደሩን የዶ/ር ሱለይማን አልሐቢብ የሕክምና አገልግሎቶች ቡድን ይመራል።
ሆስፒታሉ 44 አልጋዎች፣ 41 የተመላላሽ ሕሙማን ክሊኒኮች፣ ለጽኑ ሕሙማንና ለአራስ ሕፃናት እንክብካቤ 9 አልጋዎች እንዲሁም አንዱ ለቀዶ ሕክምና ወሊድ የተመደበ 3 የቀዶ ጥገና ክፍሎች አሉት። የድንገተኛ ሕክምናን ጨምሮ የሕክምናና የቀዶ ጥገና ስፔሻሊቲ አገልግሎቶችን ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች ይሰጣል።
ሚኒስትሩ የመንግሥቱ የቱሪዝም ዘርፍ ፈጣንና ጥራት ያለው ዕድገት እያሳየ መሆኑንና የቀይ ባሕር መዳረሻም የዚህ ዕድገት ልዩ ምሳሌ እንደሆነ ተናግረዋል። "የቀይ ባሕር ሆስፒታል መከፈት በቱሪዝም መዳረሻዎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ ትልቅ እርምጃ ነው" ብለዋል።
ምረቃው ሬድ ሲ ኢንተርናሽናልና የአልሐቢብ ቡድን በሴፕቴምበር 2025 ይፋ ያደረጉት ስትራቴጂያዊ አጋርነት ቀጣይ ነው። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሬድ ሲ ኢንተርናሽናል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጆን ፓጋኖና የአልሐቢብ ቡድን ሊቀመንበር ዶ/ር ሱለይማን ቢን አብዱልአዚዝ አልሐቢብ ተገኝተዋል።
ፕሮጀክቱ የሳዑዲ ራዕይ 2030 እና የጤና ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን የማስፋትና ከግሉ ዘርፍ ጋር ያለውን አጋርነት የማጠናከር ግቦች አካል ነው።


