የሳዑዲ ዓረቢያ የሐጅና ዑምራ ሚኒስቴር 21 የዑምራ ኩባንያዎች አገልግሎት እንዳይሰጡ አግዷል። ውሳኔው የተላለፈው ያለፈው ወቅት የአፈጻጸም ግምገማ ውጤት በርካታ ኩባንያዎች የአፈጻጸም ማሽቆልቆል እንዳሳዩና የዑምራ ተጓዦችን አገልግሎት የሚመሩ ሕጎችንና መመሪያዎችን እንደጣሱ ካሳየ በኋላ ነው።
ሚኒስቴሩ እንዳብራራው፣ እገዳው በጸደቁ የአፈጻጸም መለኪያዎች ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገቡ 15 ኩባንያዎችን እንዲሁም ሕጎችንና መመሪያዎችን የጣሱ ሌሎች 6 ኩባንያዎችን ያካትታል፤ ይህም በእነርሱ ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድን አስፈላጊ አድርጓል።
እርምጃው ለመጪው የዑምራ ወቅት የሚደረገው ቅድመ ዝግጅት አካል መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል። የግምገማ ሥርዓቱ የአገልግሎት ጥራትንና የኩባንያዎችን ሕግ አክባሪነት በሚለኩ የአሠራርና የቁጥጥር መለኪያዎች ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ዓላማውም በአገልግሎት ሰጪዎች መካከል ውድድርን ማሳደግና በሳዑዲ ራዕይ 2030 መሠረት ለዑምራ ተጓዦችና ለነቢዩ መስጊድ ጎብኚዎች ደኅንነቱ የተጠበቀና የላቀ ተሞክሮ ማቅረብ ነው።
ሚኒስቴሩ ሕጎችን በጥብቅ መተግበሩን እንደሚቀጥልና የአገልግሎት ጥራትን ወይም የአላህ እንግዶችን መብት የሚነካ ማንኛውንም ጉድለት እንደማይታገሥ አስታውቋል። ከኢትዮጵያ ዑምራ ለማድረግ ለሚያቅዱ ሰዎች ይህ ውሳኔ ከመመዝገባቸው በፊት የኩባንያውን ፈቃድና የአገልግሎት ደረጃ ማረጋገጥ ያለውን ጠቀሜታ ያስታውሳል።
