የሳዑዲ አረቢያ ሲቪል መከላከያ ጠቅላይ ዳይሬክቶሬት ነጎድጓዳማ ዝናብ በአብዛኞቹ የመንግሥቱ ክልሎች እስከ መጪው ሰኞ ስለሚቀጥል ሕዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል። ነዋሪዎች ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ እንዲቆዩ፣ ጎርፍ ከሚሰበሰብባቸው ቦታዎችና ከሸለቆዎች እንዲርቁ፣ በውስጣቸው እንዳይዋኙ እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ሚዲያ የሚወጡ ይፋዊ መመሪያዎችን እንዲከተሉ ተጠይቀዋል።
ብሔራዊ የሜትሮሎጂ ማዕከል እንዳስታወቀው፣ የመካ ክልል መካከለኛ እስከ ከባድ ዝናብ የሚያገኝ ሲሆን ይህም ድንገተኛ ጎርፍ፣ በረዶና አቧራ የሚያስነሳ ኃይለኛ ነፋስ ሊያስከትል ይችላል። ይህ ሁኔታ የመካ ከተማን፣ አል-ካሚልን፣ አል-ጁሙምን፣ በሕራን፣ ጣኢፍን፣ መይሳንን፣ አዶምንና አል-አርዲያትን ይመለከታል። በጂዳ፣ ኹለይስ፣ ራቢግ፣ አል-ሊስ፣ አል-ቁንፉዛ፣ ረኒያ፣ ቱረባ፣ አል-ኹርማና አል-ሙወይህ ደግሞ ቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ ይጠበቃል።
የጃዛን፣ አሲር፣ አል-ባሃ፣ መዲና፣ ሃኢል እና ቃሲም ክልሎችም ጎርፍ፣ በረዶና አቧራማ ነፋስ የታከለበት መካከለኛ እስከ ከባድ ዝናብ ያገኛሉ። በምሥራቃዊ ክልል፣ በታቡክ፣ በአል-ጃውፍ እና በሰሜናዊ ድንበር ክልል ቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ ይጠበቃል።
