ጃፓን አሸባሪው የሁቲ ቡድን በሳዑዲ ዓረቢያ አውሮፕላን ማረፊያዎችና የሲቪል ተቋማት ላይ በተደጋጋሚ የፈጸማቸውን ጥቃቶች አጥብቃ አውግዛለች። የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቶሺሚትሱ ሞቴጊ ይህን ያስታወቁት ከሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፈይሰል ቢን ፈርሃን ቢን አብዱላህ ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት ነው።
በሳዑዲ ወገን መግለጫ መሠረት ሁለቱ ሚኒስትሮች "አሸባሪው የሁቲ ሚሊሻ" በፈጸማቸው ጥቃቶች ላይ የተወያዩ ሲሆን፣ ሞቴጊ አገራቸው ጥቃቶቹን እንደምታወግዝ ገልጸዋል።
ሚኒስትሮቹ በሁለቱ ወዳጅ አገሮች መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ትብብር የገመገሙ ሲሆን፣ በቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይም ሐሳብ ተለዋውጠዋል።
የኃይል ደኅንነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም በቀጣናዊና ዓለም አቀፍ የውኃ መስመሮች ላይ የመርከብ ጉዞ ነፃነትንና ደኅንነትን ለመጠበቅ ቅንጅትና ትብብርን ማሳደግ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይም ተነጋግረዋል።
