የሳውዲ አረቢያ አልጋ ወራሽና ጠቅላይ ሚኒስትር ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን ቢን አብዱልአዚዝ አል ሱዑድ በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ በሚገኘው አል-ኢቲሓዲያ ቤተ መንግሥት ከዐረብ ሪፐብሊክ ግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታሕ አል-ሲሲ ጋር ተገናኝተዋል። የሳውዲ ፕሬስ ኤጀንሲ (SPA) እንደዘገበው፣ ሁለቱ መሪዎች የሁለትዮሽ ስብሰባና ሰፊ የውይይት መድረክ አካሂደዋል።
ፕሬዚዳንት አል-ሲሲ አልጋ ወራሹን “ሁለተኛ አገራቸው” ወደሆነችው ግብፅ እንኳን ደህና መጡ ያሉ ሲሆን፣ አልጋ ወራሹም ለእሳቸውና ለልዑካን ቡድናቸው ለተደረገው ደማቅ አቀባበልና መስተንግዶ ምስጋና አቅርበዋል።
በውይይቱ የሁለቱ ወንድማማች አገሮች ስትራቴጂያዊ የሁለትዮሽ ግንኙነትና በተለያዩ መስኮች ግንኙነቱን የማሳደግ መንገዶች ተገምግመዋል። በተጨማሪም የዐረብና የእስላማዊው ዓለም ጉዳዮች፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ሁኔታዎች፣ በተለይም የባሕር ጉዞ ደኅንነትንና ነፃነትን ጨምሮ የቀጣናው ደኅንነትና መረጋጋት እንዲሁም በዚህ ረገድ ጥረቶችን ማቀናጀት ተነስተዋል።
ከሳውዲ ወገን በስብሰባው ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ልዑል ፈይሰል ቢን ፈርሓን ቢን አብዱላህ፣ የመንግሥት ሚኒስትር፣ የካቢኔ አባልና የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ዶ/ር ሙሳዒድ ቢን መሐመድ አል-ዒባን፣ የመንግሥት ሚኒስትርና የሹራ ምክር ቤት ጉዳዮች የካቢኔ አባል ዶ/ር ዒሳም ቢን ሰዕድ ቢን ሰዒድ እንዲሁም የአልጋ ወራሹ ጸሐፊ ዶ/ር በንደር ቢን ዑበይድ አል-ረሺድ ተገኝተዋል።
ከግብፅ ወገን የውጭ ጉዳይ፣ የዓለም አቀፍ ትብብርና በውጭ የሚኖሩ ግብፃውያን ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር በድር አብዱልዓጢ፣ የጠቅላላ የመረጃ አገልግሎት ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ሐሰን ረሻድ፣ የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ዑመር መርዋንና የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ አምባሳደር መሐመድ አል-ሸናዊ ተገኝተዋል።


