በኢንዶኔዥያ የጋራ የፍለጋና የነፍስ አድን ቡድኖች የምዕራብ ሱማትራ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ፓዳንግ በጎርፍ ውኃ ከተዋጡ ሁለት ቦታዎች ከ50 በላይ ነዋሪዎችን ወደ ደኅንነቱ የተጠበቀ ቦታ አስወጥተዋል።

የኢንዶኔዥያው የዜና ወኪል አንታራ እንደዘገበው ከቅዳሜ ቀትር ጀምሮ የጣለው ከባድ ዝናብ የወንዞችን መጠን ከፍ በማድረግ ከአቅማቸው በላይ እንዲፈሱ አድርጓል፤ በዚህም በከተማዋ ሁለት አካባቢዎች ጎርፍ ተከስቷል።

ጭቃ የቀላቀለው ቡናማ ውኃ በፈጣን ፍሰት ወደ መኖሪያ መንደሮች የገባ ሲሆን ከፍታውም ከ50 ሴንቲሜትር በላይ ደርሷል ተብሏል።

የፓዳንግ የፍለጋና የነፍስ አድን ጽሕፈት ቤት የመስክ ቡድን መሪ ከሥራው በኋላ "የጎርፉ ውኃ ከፍተኛና በፍጥነት የሚፈስ ነበር፤ በዚህም በአሥሮች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተከበው ለመውጣት እርዳታ አስፈልጓቸዋል" ብለዋል። የነፍስ አድን ሠራተኞቹ የላስቲክ ጀልባዎችንና በውኃው ላይ የተዘረጉ ገመዶችን ተጠቅመዋል።