የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ አገራቸው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያወጁትን በኢነርጂ ዘርፍ ላይ ያተኮረ የተኩስ አቁም እንደምትደግፍ አስታውቀዋል።
ዘለንስኪ በማኅበራዊ ሚዲያ ባሰፈሩት መልዕክት ከካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ፣ ከፊንላንዱ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ስቱብና ከኔቶ ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩተ ጋር አሁን ውይይት ማድረጋቸውንና በኢነርጂ ዘርፉ የተኩስ አቁም ላይ መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
"ዩክሬን ይህን የተኩስ አቁም ትደግፋለች፤ ሩሲያም እንድትደግፈው ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው" ያሉት ዘለንስኪ፣ ዩክሬን ከአሜሪካ ወገን ዝርዝር መረጃ እየጠበቀች መሆኗንም ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ዩክሬን ውጥረትን ለማርገብና ሕይወትን ለመጠበቅ የሚወሰዱ እርምጃዎችን እንዲሁም ጦርነቱን ለማቆምና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያስፈልጉ ውሳኔዎችን ሁልጊዜም ሙሉ በሙሉ እንደምትደግፍ አስረግጠው ተናግረዋል።
