የመስጂደል ሐራም ኢማምና ኸጢብ ሼኽ ዶ/ር ዐብዱራሕማን ቢን ዐብዱልዐዚዝ አል-ሱደይስ በጁምዓ ኹጥባቸው ሙስሊሞች ማኅበራዊ ሚዲያንና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ሲጠቀሙ ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ገደቦችን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል። አሉባልታና አሳሳች ዜናዎችን ከማሰራጨትና የሌሎችን ግላዊነት ከመጣስ እንዲጠነቀቁም አሳስበዋል።
ኢስላም መልካም ሥነ ምግባርን የሚመራ የተሟላ የሕይወት ሥርዓት መሆኑን ገልጸው፣ ማኅበራዊ ሚዲያና ሰው ሠራሽ አስተውሎት በአግባቡ በመጠቀም ምስጋና የሚቀርብባቸው ጸጋዎች መሆናቸውን ተናግረዋል። ሰው በዲጂታል መድረኮች የሚጽፈውም ሆነ የሚያጋራው ሁሉ የሚጠየቅበት መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ለማጭበርበር፣ የሐሰት ቪዲዮ ለመሥራት፣ ድምፅ ለመኮረጅና የሌላ ሰውን ማንነት ለመላበስ መጠቀም የተከለከለ ውሸትና በሰዎች ክብር ላይ የሚፈጸም ጥቃት መሆኑን ገልጸዋል። ዜናዎችን፣ ምስሎችንና ቪዲዮዎችን ከማጋራት በፊት ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበው የነቢዩን ሐዲስ ጠቅሰዋል፦ 'ሰው የሰማውን ሁሉ ማውራቱ ውሸታም ለመሆን በቂው ነው።'
በሁለተኛው ኹጥባ አንድነትን አበረታተው ከማስፈራራት፣ ከስም ማጥፋት፣ ከኢንተርኔት ማጭበርበርና በፍጥነት ሀብታም መሆንን ከሚያስተዋውቁ የሐሰት መልእክቶች እንዲሁም መሪዎችንና ዑለማዎችን ዒላማ ካደረጉ የሐሰት ቪዲዮዎች እንዲጠበቁ መክረዋል።
አሸባሪው የሁቲ ሚሊሻ በመካና በመዲና ላይ የፈጸማቸውን የወንጀልና የሽብር ጥቃቶች አውግዘው፣ ጥቃቶቹ ከሸሪዓ ጋር የሚጋጩ፣ የሙስሊሞችን ስሜት የሚያነሳሱና ዓለም አቀፍ ደንቦችንና ስምምነቶችን በግልጽ የሚጥሱ መሆናቸውን ተናግረዋል። የሁለቱ ቅዱሳን መስጂዶች ደኅንነትና ቅድስና ሊታለፍ የማይችል ቀይ መስመር መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።


