ፓኪስታን የሁቲ ሚሊሻ በቅድስቲቱ መዲና ከተማ በሚገኘው የ‹ጠይባ› የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ የፈጸመውን ጥቃት አጥብቃ አውግዛለች። ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ሙሉ አጋርነቷንና ለመንግሥቱ ደኅንነት፣ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ያላትን ድጋፍ መግለጿን የሳዑዲ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።
የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ በእ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር 29 ለነቢዩ መስጊድ ኤሌክትሪክ በሚያቀርብ ሲቪል ተቋም ላይ የተፈጸመው ጥቃት ከባድ ትንኮሳ መሆኑንና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሙስሊሞች ጥልቅ ስጋትና ሐዘን መፍጠሩን ገልጿል።
ሚኒስቴሩ የሁለቱ ቅዱሳን መስጊዶች ክብር በማንኛውም ሁኔታ መከበር እንዳለበትና የሰጋጆች፣ የሐጅና የዑምራ ተጓዦች ደኅንነት መረጋገጥ እንዳለበት አሳስቧል። ለክልላዊ ሰላምና ደኅንነት ከባድ ስጋት ናቸው ያላቸው እንዲህ ያሉ ድርጊቶች በአስቸኳይና ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲቆሙም ጠይቋል።
ፓኪስታን ቅዱሳን መስጊዶችን፣ የሳዑዲን ሕዝብና የሐጅና የዑምራ ተጓዦችን በመጠበቅ ረገድ ከመንግሥቱ ጎን እንደምትቆም በድጋሚ ያረጋገጠች ሲሆን፣ በቀጠናው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ጥረቷን እንደምትቀጥል አስታውቃለች።
