የእስላማዊ ልማት ባንክ ተቋምና ዓለም አቀፍ የፖስታ ኅብረት (UPU) «የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ብልጽግና» የተሰኘ ፕሮጀክት ለመጀመር ስምምነት ተፈራርመዋል። ፕሮጀክቱ በባንኩ አባል ሀገራት የሚገኙ ብሔራዊ የፖስታ መረቦች የኢ-ኮሜርስ ተደራሽነትን እንዲያሰፉና ከሸሪዓ ጋር የሚጣጣሙ ዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ በማስቻል አነስተኛ ንግዶችንና የፋይናንስ አገልግሎት ያልደረሳቸውን ማኅበረሰቦች ለመደገፍ ያለመ ነው።

ስምምነቱን የተቋሙ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር እና የUPU ዓለም አቀፍ ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ፈርመውታል። ትብብሩ የፖስታ መሠረተ ልማትን ለመጠቀም፣ አነስተኛ ንግዶች በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግና ድንበር ተሻጋሪ ንግድን ለማቀላጠፍ ያለመ ነው።

ፕሮጀክቱ ከባንኩ አባል ሀገራት በተመረጡ ስምንት ሀገራት በሁለት ምዕራፎች ይተገበራል። የመጀመሪያው ምዕራፍ የኢ-ኮሜርስ፣ የፖስታ አገልግሎቶች፣ የዲጂታል ክፍያዎችና የእስላማዊ ፋይናንስ የቁጥጥር ማዕቀፎችን ይገመግማል፤ ሁለተኛው ደግሞ በገበያ ትንተና፣ አነስተኛ ንግዶች ኢ-ኮሜርስን ሲቀበሉ የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በመለየትና የፋይናንስ ክፍተቶችን፣ የገበያ ፍላጎቶችንና የፖስታ መረቦችን አቅም በማጥናት ላይ ያተኩራል።

ፕሮጀክቱ የፖስታ መሠረተ ልማትን በመጠቀም ለኢ-ኮሜርስ፣ ለክፍያና ለእስላማዊ ፋይናንስ አገልግሎቶች አዳዲስ መፍትሔዎችን ያዘጋጃል፤ በተለይም የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን፣ የሴቶችንና የወጣቶችን ፍላጎቶች ትኩረት ይሰጣል።

የፕሮጀክቱን ወጪ የእስላማዊ ልማት ባንክ ተቋም የሚሸፍን ሲሆን UPU ቴክኒካዊ ልምዱን፣ የመረጃ ቋቶቹንና ዓለም አቀፍ የፖስታ ግንኙነቶቹን ያቀርባል። ፕሮጀክቱ በስምንቱ ሀገራት የተደረጉ ጥናቶችን ውጤትና የትግበራ ፍኖተ ካርታን የያዘ አጠቃላይ ሪፖርት በማዘጋጀት ይጠናቀቃል።