የዓለም የሕዋ ሳምንትን ምክንያት በማድረግ በሳዑዲ ዓረቢያ የአልዑላ አውራጃ ከተለያዩ የዓለም አገሮች የመጡ ቱሪስቶችንና ከዋክብትን መመልከት የሚወዱ ጎብኚዎችን በብዛት እያስተናገደ ነው። የተፈጥሮ ሀብቱ፣ ጥርት ያለው ሰማዩና ዝቅተኛው የብርሃን ብክለት አልዑላን ቀዳሚ የሥነ ፈለክ ቱሪዝም መዳረሻ አድርገውታል።

ጎብኚዎች ከዋክብትን መመልከትና ፎቶ ማንሳት፣ በቴሌስኮፕ ፕላኔቶችንና ሌሎች የሰማይ አካላትን መከታተል እንዲሁም ከጥንት እስከ ዛሬ ከሥነ ፈለክ ጋር የተያያዙ ባህላዊ ቅርሶችንና ታሪኮችን ማወቅ ይችላሉ።

የአልዑላ የተለያዩ የተፈጥሮ ሥፍራዎች፣ ልዩ የአለት ቅርጾችና የበረሃ መልክዓ ምድሮች ጎብኚዎች ተፈጥሮን እያሰሱ ውበቷን እንዲያጣጥሙ ዕድል ይሰጣሉ።

ብቃት ባላቸው ወጣት ሳዑዲ ወንዶችና ሴቶች ባለቤትነት የተያዙ የአካባቢው አስጎብኚ ድርጅቶች እንግዶችን ተቀብለው የተለያዩ ጉብኝቶችን ያዘጋጃሉ፤ ወንድና ሴት አስጎብኚዎችም የአልዑላን ጥንታዊና ተፈጥሯዊ መስህቦች በበርካታ ቋንቋዎች ያስተዋውቃሉ።

በአልዑላ የሚገኙ በርካታ ሥፍራዎች ከዓለም አቀፉ የጨለማ ሰማይ ድርጅት (DarkSky International) ዕውቅና አግኝተዋል፤ ይህም አካባቢን ለመጠበቅና የብርሃን ብክለትን ለመቀነስ የተደረገውን ጥረት የሚያሳይ ነው። «የአልዑላ ማናራ» ቡድንም በሥነ ፈለክና በሕዋ ሳይንስ ባለሙያዎች የሚመሩ የምልከታ መርሐ ግብሮችንና አሳታፊ ዎርክሾፖችን ያቀርባል።