የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ (ኤስፒኤ) እንደዘገበው፣ የመካ ከተማና የቅዱሳን ሥፍራዎች ንጉሣዊ ኮሚሽን በመካ የመንገድ መረብ ልማት ፕሮጀክቶች አካል የሆኑ በርካታ መስመሮችን ለትራፊክ ክፍት አድርጓል። እነዚህም ሦስተኛውን የቀለበት መንገድና የልዑል ሳዑድ አል-ፈይሰል መንገድን ያካትታሉ።
በሦስተኛው የቀለበት መንገድ ላይ ከልዑል ሙትዒብ መገናኛ በልዑል ሱልጣን መገናኛ በኩል እስከ ታላቁ መስጊድ (አል-መስጂድ አል-ሐራም) መገናኛ የሚዘልቅ ተጨማሪ 1.5 ኪሎ ሜትር አዲስ መስመር ተከፍቷል። ይህ የሦስተኛውን የቀለበት መንገድ ቀሪ ክፍሎች የማጠናቀቅ ፕሮጀክቶች አካል ነው።
ከልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን ጎዳና ለሚመጡ ተሽከርካሪዎችም የልዑል ሳዑድ አል-ፈይሰል መንገድ ቀሪ መስመር ተከፍቷል። መስመሩ በልዑል ናይፍ ቢን አብዱልአዚዝ መገናኛ በኩል እስከ አብዱልቃዲር ኩሻክ ጎዳና የሚዘልቅ ሲሆን፣ በአቅራቢያው ያለውን ሰፈር ነዋሪዎች ያገለግላል።
እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ፣ እነዚህ ሁለት ሥራዎች የትራፊክ ፍሰትን ለማቀላጠፍ፣ የመንገድ ደኅንነትን ለማሳደግና በሦስተኛው የቀለበት መንገድ ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ ያግዛሉ፤ የጉዞና የእንቅስቃሴ ጊዜንም ከ90% በላይ ያሳጥራሉ።
ይህም ነዋሪዎችን ብቻ ሳይሆን በሐጅና በዑምራ ወቅቶች የሚመጡ ምዕመናን ሰፈሮችንና ቅዱሳን ሥፍራዎችን በቀላሉ እንዲደርሱ ያስችላል።


