የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ (SPA) እንደዘገበው፣ የ2026 ዓለም አቀፍ የሳዑዲ ጭልፊትና አደን ኤግዚቢሽን ሐሙስ ዕለት ከሪያድ በስተሰሜን በማልሐም በሚገኘው የሪያድ ኤግዚቢሽንና ኮንቬንሽን ማዕከል ተከፍቷል። በብሔራዊ የጭልፊት ማዕከል የተዘጋጀው ኤግዚቢሽኑ እስከ ኦክቶበር 10 የሚቆይ ሲሆን 'ለሁሉም የሚሆን ተሞክሮ' በሚል መሪ ቃል የጭልፊት፣ የአደን፣ የጀብዱ፣ የጉዞና የባህል ተሞክሮዎችን ያቀርባል።
የብሔራዊ የጭልፊት ማዕከል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጠላል ቢን ዐብዱልዐዚዝ አል-ሹማይሲ የኤግዚቢሽኑ መስፋፋት አመራሩ ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ውጤት መሆኑንና ይህም ቅርሱን ለመጠበቅና ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እንደረዳ ተናግረዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ ኤግዚቢሽኑ በዓለም በዓይነቱ ትልቁ ተብሎ ይመደባል።
ዝግጅቶቹ 'የወደፊቱ ጭልፊት አሳዳጊ'፣ ቀስትና የአየር ጠመንጃ ተኩስ፣ የባለአራት እግር ተሽከርካሪ ጉዞ፣ የባሕር አደን፣ የእግር ጉዞ፣ ባህላዊ ትርዒቶች፣ የጭልፊት ጨረታና አውደ ጥናቶችን ያካትታሉ። ከኦክቶበር 4 እስከ 9 የሚካሄደው 'አል-ሙልዋሕ' የጭልፊት ውድድር ዘንድሮ ወደ 12 ዙሮች ያደገ ሲሆን በእያንዳንዱ ዙር ለመጀመሪያዎቹ አምስት ደረጃዎች በድምሩ 723 ሺህ ሪያል ሽልማት ይከፋፈላል።
ኤግዚቢሽኑ በሳዑዲ አረቢያ የመጀመሪያውና ብቸኛው የጦር መሣሪያ፣ የጥይትና የመለዋወጫ ክፍል ያለው ሲሆን ከ181 በላይ ዓለም አቀፍ ብራንዶች ከአምስት ሺህ በላይ ምርቶች ቀርበዋል። ዘንድሮ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የአጥ-ጡረይፍ መንደር ልዩ ትኩረት አግኝቷል።
ኤግዚቢሽኑ በየቀኑ ከሰዓት በኋላ 2:00 እስከ ምሽቱ 11:00 (በአውሮፓውያን የሰዓት አቆጣጠር) ክፍት ነው። ከተለያዩ የሪያድ አካባቢዎች ቀንና ሌሊት የሚሠሩ የማመላለሻ አውቶቡሶች አሉ፤ መስመሮቻቸውና ሰዓቶቻቸው በማዕከሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ይገኛሉ።



