የሐጃጆች ወደ ቅድስቲቱ መካ የሚያደርጉት ጉዞ ዋና ከተማዋን ከተለያዩ የመንግሥቱ ክልሎች ጋር በሚያገናኙ ዋና ዋና መንገዶች መረብ ላይ የተመሠረተ መሆኑን የሳዑዲ ዓረቢያ የመንገዶች ጠቅላላ ባለሥልጣን አስታውቋል። መንገዶቹ በሐጅ ወቅት እንቅስቃሴን በማቅለልና የመድረሻ ብቃትን በማሳደግ ረገድ ሚና አላቸው።
ከእነዚህ መንገዶች ቀዳሚው ቅድስቲቱን መዲናና መካን የሚያገናኘው 420 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የሂጅራ መንገድ ነው። መንገዱ የተቀደሰውን መስጊድ ከነቢዩ መስጊድ ጋር ስለሚያገናኝ በወቅቱ በጣም ከተጨናነቁ መንገዶች አንዱ ነው።
ከደቡብ በኩል 90 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የለይስ መንገድ የመንግሥቱን ደቡባዊ ክልሎች ከመካ ጋር ያገናኛል። 80 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአስ-ሰይል አል-ከቢር መንገድ የጣኢፍ አውራጃን ከመካ ጋር ሲያገናኝ፣ 23 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የዐቀበት አል-ሀዳ ተራራማ መንገድም ሁለቱን ያገናኛል። ከዘመናዊዎቹ መንገዶች አንዱ የሆነው የልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን መንገድ ደግሞ ጂዳን ከመካ ጋር በ70 ኪሎ ሜትር ያገናኛል።
ባለሥልጣኑ እነዚህ መንገዶች በመካ መግቢያዎች ላይ የደኅንነትና የሥራ ብቃት ደረጃን ከፍ የሚያደርግ የተሳሰረ መረብ አካል መሆናቸውን ገልጿል። እየጨመረ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላትና የመንገድ ዘርፍ ፕሮግራም ግቦችን ለማሳካት መረቡን በከፍተኛ ደረጃዎች ማልማቱን እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
