የሳዑዲ ዓረቢያ የእስልምና ጉዳዮች፣ የዳዕዋና የመመሪያ ሚኒስቴር በሚና ቅዱስ ስፍራ የሚገኘውን የአል-ኸይፍ መስጊድ በ1447 ዓ.ሂ. የሐጅ ወቅት የተርዊያ ቀን የአላህ እንግዶችን ለመቀበል የሚያስችለውን ዝግጅት አጠናቋል።
የመስጊዱ ሕንፃ 23,500 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን፣ በምርጥ ምንጣፍ የተሸፈነው ቦታ ከ27 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ ነው። ብዙ ሕዝብ ለማስተናገድ መገልገያዎቹ ተሻሽለዋል፤ በዘመናዊ የቁጥጥር ሥርዓት የሚተዳደሩ 410 የማቀዝቀዣ ክፍሎችም ተገጥመውለታል።
በቅርብ ዓመታት ከተከናወኑት የልማት ፕሮጀክቶች መካከል በመስጊዱና በመጸዳጃ ቤቶቹ ዙሪያ አየሩን የሚያቀዘቅዘው ፕሮጀክት ይገኝበታል፤ በዚህም የሙቀት ድካምን ለመቀነስ በአደባባዮች፣ በመተላለፊያዎችና በኮሪደሮች 57 የውሃ ርጭት ማራገቢያዎች ተተክለዋል። ሚኒስቴሩ እያንዳንዳቸው በሰዓት 500 ሊትር የሚያመርቱ 54 የውሃ ማቀዝቀዣዎችን የያዘ የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት ተግባራዊ አድርጓል፤ በአጠቃላይ በሰዓት ከ81 ሺህ በላይ ሐጃጆችን ያገለግላሉ። የሞባይል ስልክ መሙያ አገልግሎትም ተዘጋጅቷል።
በናሚራና በአል-ኸይፍ መስጊዶች የአየር ማቀዝቀዣን፣ የአየር ዝውውርን፣ ኤሌክትሪክንና ተጠባባቂ ጀነሬተሮችን የሚቆጣጠር ዘመናዊ ሥርዓት ተዘርግቷል። መስጊዱ በተለያዩ ቋንቋዎች የግንዛቤ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ 79 ዲጂታል ስክሪኖች፣ ከ50 በላይ የክትትል ካሜራዎች፣ 9 ዋና መግቢያዎችና 6 የአደጋ ጊዜ መውጫዎች አሉት። ከ500 በላይ ሠራተኞች፣ ቴክኒሻኖችና ሌሎች ባለሙያዎች ቀንና ሌሊት ይሠራሉ።
የእስልምና ጉዳዮች፣ የዳዕዋና የመመሪያ ሚኒስትር ሸይኽ ዶ/ር ዓብዱለጢፍ ቢን ዓብዱልዐዚዝ አል-ሸይኽ መስጊዱን በአካል ጎብኝተው፣ ሚኒስቴሩ የአመራሩን መመሪያ በመተግበር ሐጃጆችን ለማገልገል ሙሉ አቅሙን እያዋለ መሆኑን አረጋግጠዋል።


