የማዘጋጃ ቤቶችና የቤቶች ሚኒስቴር በቅድስቲቱ መካ ማዘጋጃ ቤት በኩል ከዛሬ ጀምሮ ሐጃጆችን ለመቀበል የዓረፋትን ቅዱስ ስፍራ የማዘጋጀት ሥራ አጠናቋል። ዝግጅቱ መንገዶችን፣ የመብራት መረቦችን፣ የሕዝብ መገልገያዎችን፣ ንጽሕናንና የአካባቢ ጤናን ያካትታል።
ማዘጋጃ ቤቱ ስፍራውን በሙሉ ለመሸፈንና ሠራተኞችንና መሣሪያዎችን በብቃት ለማሰማራት ዓረፋትን በመልክዓ ምድር የተከፋፈሉ ሦስት የአገልግሎት ማዕከላት አድርጎ ከፍሎታል። ሙዝደሊፋም በሦስት ዞኖች ተከፍሏል፤ እነርሱም ደቡብ ሙዝደሊፋ፣ አል-መሽዓር አል-ሐራምና ሰሜን ሙዝደሊፋ ሲሆኑ፣ ለመመላለሻ ትራንስፖርት የተመደቡ የሕዝብ ትራንስፖርት ቦታዎችም ተዘጋጅተዋል።
እያንዳንዱ ዞን በአንድ መሪ ኃላፊና ረዳት የሚመራ የመስክ ተቆጣጣሪ ቡድን ተመድቦለታል። የማዕከላቱ ኃላፊዎች ከጠቅላላ ቁጥጥሩ ጋር በመቀናጀት እንደ አስፈላጊነቱ የሥራ ማስተካከያዎችን የማድረግ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል።
ማዘጋጃ ቤቱ ከ88,000 በላይ የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎችንና ክፍሎችን አዘጋጅቷል፤ እንዲሁም 1,235 የቆሻሻ መጨመቂያ ሳጥኖችንና 113 የምድር ውስጥ ጊዜያዊ ማከማቻዎችን ሥራ ላይ አውሏል። ይህም በከፍተኛ የሰዎች ብዛት ወቅት የመሣሪያዎች እንቅስቃሴ ችግርን ለማቃለል ያለመ ነው።
ዕቅዶቹ የሕዝቡን ብዛት ከግምት ያስገቡ ሲሆን፣ የእግረኞችንና የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ሳያስተጓጉሉ የተበተኑ ቆሻሻዎችን ለመሰብሰብ ከትላልቅ መሣሪያዎች ይልቅ ትናንሽ መሣሪያዎችና ልዩ የእጅ ጋሪዎች ጥቅም ላይ ውለዋል። ይህ ዝግጅት ከኢትዮጵያ የሚሄዱትን ጨምሮ ከመላው ዓለም ለሚመጡ ሐጃጆች የሚያገለግል ነው።
