የሳዑዲ አረቢያ የማዘጋጃ ቤቶችና የቤቶች ሚኒስቴር የመስክ ቡድኖች በመካ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በኩል ሐጃጆች ወደ ዐረፋት እንደተንቀሳቀሱ በሚና የጽዳትና የአካባቢ ንጽሕና ሥራ ጀምረዋል። ይህ የ1447 ሂጅራ የሐጅ ወቅት የሥራ ዕቅድ አካል ሲሆን፣ ዓላማውም ከሙዝደሊፋ ለሚመለሱ ሐጃጆች ሚና ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ ነው።
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው ቡድኖቹ መላውን ሚና ቀደም ብለው በድጋሚ አዘጋጅተዋል። የቆሻሻ ማንሳት ሥራ የተጠናከረ ሲሆን፣ የመምጠጫ ፓምፖች፣ ታንከሮችና የመስክ ተሽከርካሪዎች የያዙ ተጨማሪ ቡድኖች እንደ ዝናብና እሳት ያሉ ድንገተኛ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ሌት ተቀን ሠርተዋል።
የመካ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በመካና በቅዱሳት ስፍራዎች ከ13 ሺህ በላይ ሠራተኞችን አስፈላጊ መሣሪያዎችና ማሽኖች አሟልቶ ማሰማራቱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፤ ይህም በሐጅ ወቅቱ ሁሉ ከፍተኛ የንጽሕና ደረጃ ለመጠበቅ ነው።
በቆሻሻ አስተዳደር ሥርዓቱ መሠረት ቆሻሻ በቅዱሳት ስፍራዎች ዙሪያ ወደሚገኙ የማስተላለፊያ ጣቢያዎች ይጓጓዛል። ከዐረፋት ቀን በኋላ እያንዳንዳቸው 8 ቶን በሚይዙ ከ1230 በላይ የማመቂያ ሳጥኖች ውስጥ ይከማቻል። በተጨማሪም በአጠቃላይ ወደ 2,825 ቶን የመያዝ አቅም ያላቸው ከ110 በላይ የመሬት ውስጥ ማከማቻዎች አሉ።
ሚኒስቴሩ የቆሻሻ አሰባሰብን ውጤታማ ለማድረግና አካባቢውን ንጹሕ ለመጠበቅ በቅዱሳት ስፍራዎች ወደ 88,000 የሚጠጉ የቆሻሻ ማስቀመጫዎች መዘጋጀታቸውንም ገልጿል።

