የሳዑዲ አረቢያ ሲቪል መከላከያ ጠቅላይ ዳይሬክቶሬት ሕዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ፣ ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ እንዲቆይ፣ ከሸለቆዎችና የጎርፍ ውሃ ከሚሰበሰብባቸው ቦታዎች እንዲርቅና በውስጣቸው እንዳይዋኝ ጥሪ አቅርቧል። በመገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ መመሪያዎችን እንዲከተልም አሳስቧል፤ ምክንያቱም ነጎድጓዳማ ዝናቡ በአብዛኞቹ የመንግሥቱ ክልሎች እስከ ቅዳሜ ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።
ብሔራዊ የሜትሮሎጂ ማዕከል እንዳስታወቀው፣ የመካ ክልል ከመካከለኛ እስከ ከባድ ዝናብ፣ ድንገተኛ ጎርፍ፣ በረዶና አቧራ የሚያስነሳ ኃይለኛ ነፋስ ይኖረዋል። ይህም መካ ከተማን፣ አል-ካሚልን፣ አል-ጁሙምን፣ በሕራን፣ ጣኢፍን፣ መይሳንን፣ አድሐምንና አል-ዐርዲያትን ያካትታል። በጅዳ፣ ራቢግ፣ ኹለይስ፣ አል-ሊስ፣ አል-ቁንፉዛ፣ ረኒያ፣ አል-ኹርማ፣ አል-ሙወይህና ቱረባ ደግሞ ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ ይጠበቃል።
በሪያድ ክልል በዋዲ አድ-ደዋሲር፣ አስ-ሱለይል፣ ዐፊፍ፣ አል-ቁወይዒያ፣ አር-ረይንና አድ-ደዋድሚ ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ ከጎርፍ፣ ከበረዶና ከአቧራማ ነፋስ ጋር ይጠበቃል።
የጃዛን፣ የዐሲርና የአል-ባሓ ክልሎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ ዝናብ የሚያገኙ ሲሆን፣ መዲና፣ የምሥራቅ ክልል፣ ሓኢል፣ ታቡክ፣ አል-ጀውፍ፣ የሰሜን ድንበር ክልልና ናጅራን ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ ይኖራቸዋል።
