የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የኤል ኒኞ ክስተት እየተጠናከረ ሄዶ በመጪው ዲሴምበር ከፍተኛ ደረጃው ላይ እንደሚደርስና እስከ ፌብሩዋሪ 2027 እንደሚቆይ ተንብዮአል። ድርጅቱ ይህ ክስተት ከ1950 ወዲህ ከተመዘገቡት እጅግ ጠንካራ የኤል ኒኞ ክስተቶች አንዱ ሊሆን እንደሚችል ገልጿል።

እንደ ድርጅቱ ገለጻ ከኦክቶበር እስከ ዲሴምበር ባለው ጊዜ በምድር ወገብ አካባቢ በሚገኘው የፓሲፊክ ውቅያኖስ መካከለኛና ምሥራቃዊ ክፍሎች የባሕር ገጽ ሙቀት ከመደበኛው በ3.7 ዲግሪ ሴልሺየስ ሊበልጥ ይችላል። ይህም በኖቬምበር 2015 እና በጃንዋሪ 2016 መካከል የተመዘገበውን የ2.6 ዲግሪ የቀድሞ ሪከርድ የሚያልፍ ይሆናል።

የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ሴሌስት ሳውሎ በወርሃዊ የአየር ንብረት ትንበያዎች መሠረት ክስተቱ እስከ ፌብሩዋሪ 2027 የመቀጠሉ ዕድል 100 በመቶ ገደማ መሆኑን አስታውቀዋል።