የሪያድ ከተማ ንጉሣዊ ኮሚሽን ከልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን መንገድ ጋር በሚገናኝበት ቦታ የሚገኘው የሱማማ መንገድ ድልድይ ዋና ሥራዎች በስድስት ወራት ገደማ መጠናቀቃቸውን አስታውቋል። ድልድዩ ዓርብ ኦክቶበር 9 ከጠዋቱ 6 ሰዓት ጀምሮ ለተሽከርካሪዎች ክፍት ይሆናል።

የቀድሞው ድልድይ ከተነሳ በኋላ ግንባታው ኤፕሪል 1 ቀን 2026 የተጀመረ ሲሆን፣ መሠረት፣ የመዋቅር ሥራ፣ የድልድዩ ክፍሎች ተከላ፣ አስፋልት፣ መብራትና የማጠናቀቂያ ሥራዎችን አካትቷል። ቦታው ብዙ ትራፊክ ያለበት፣ ጠባብና ከሪያድ ሜትሮ ምሰሶዎች አጠገብ በመሆኑ በልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን መንገድ ላይ በአጠቃላይ ከ3200 ቶን በላይ የሚመዝኑ የመዋቅር ክፍሎች ትራፊክ ሳይቋረጥ ተነስተው ተገጥመዋል። ሥራው ያለ ምንም ጉዳት ወይም አደጋ ተጠናቋል።

ድልድዩ ወደ 400 ሜትር ርዝመትና ወደ 20 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ በእያንዳንዱ አቅጣጫ ሦስት በድምሩ ስድስት ዋና መስመሮች እንዲሁም በእያንዳንዱ አቅጣጫ ሁለት በድምሩ አራት የአገልግሎት መስመሮች አሉት።

ድልድዩ በሱማማ መንገድ ላይ የምሥራቅ-ምዕራብ እንቅስቃሴን የሚያሻሽልና ወደ ንጉሥ አብደላ የፋይናንስ ዲስትሪክት፣ ዋና ዋና መንገዶችና አጎራባች የመኖሪያና የንግድ አካባቢዎች መድረስን የሚያቀል ነው። የአገልግሎት መስመሮቹ አላፊውን ትራፊክ ከአካባቢው ትራፊክ ይለያሉ።

ድልድዩ ከምሥራቅ ሼክ ጃቢር አል-ሳባሕ መንገድ እስከ ምዕራብ ንጉሥ ኻሊድ መንገድ ድረስ 24 ኪሎ ሜትር የሚዘረጋው የሱማማ መንገድ ኮሪደር ልማት አካል ሲሆን፣ ልማቱ 17 ድልድዮችን፣ 10 ዋሻዎችንና 3 መገናኛዎችን ያካትታል።

ኮሪደሩ በአራት ቡድኖች ከ22 በላይ ፕሮጀክቶችን የያዘውና ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ የከተማዋን የመንገድ መረብ ለማልማት ያለመው የሪያድ የቀለበትና ዋና መንገዶች ልማት ፕሮግራም አካል ነው።