የሳውዲ ፕሬስ ኤጀንሲ እንደዘገበው፣ ብሔራዊው አየር መንገድ "የዐረቢያ አቪዬሽን ኅብረት" (ተሐሉፍ አል-ዐረቢያ ሊጥ-ጠይራን) ከደማም ንጉሥ ፈሃድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ሪያድ የመጀመሪያ በረራውን በማድረግ ከከተማዋ ሥራውን ጀምሯል። አየር መንገዱ 24 የአገር ውስጥና 57 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ያለመ ሲሆን እስከ 2030 በዓመት ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ መንገደኞችን ለማጓጓዝ አቅዷል።
የደማም አውሮፕላን ማረፊያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር መሐመድ ቢን ዓሊ አል-ሐስኒ የመክፈቻ በረራው የምሥራቃዊ ግዛትን የአየር ትስስር ለማጠናከርና የመንገደኞችን አማራጮች ለማስፋት ጠቃሚ ምዕራፍ መጀመሩን እንደሚያመለክት ገልጸዋል፤ ይህም በብሔራዊ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ስትራቴጂ ሥር ያለውን የአቪዬሽን ፕሮግራም ግቦች ይደግፋል።
የኤር ዐረቢያ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዓዲል አል-ዓሊ ጅማሮው ለግሩፑ ጠቃሚ ምዕራፍ መሆኑንና ከምሥራቃዊ ግዛት ተመጣጣኝና አስተማማኝ የጉዞ አማራጮችን በማቅረብ ለመንግሥቱ የአቪዬሽን ዘርፍ ፈጣን ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ሥራው በሦስት ዋና ዋና የአገር ውስጥ መዳረሻዎች መጀመሩንም ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት አየር መንገዱ በአሁኑ ጊዜ ከደማም ወደ ሪያድና ወደ ጅዳ በየቀኑ ሁለት ሁለት ቀጥታ በረራዎችን፣ ወደ መዲና ደግሞ በየቀኑ አንድ ቀጥታ በረራ ያካሂዳል። ከ2,400 በላይ ቀጥተኛ ሥራዎችን ለመፍጠር፣ የአገር ውስጥ ምርትን ለመደገፍና በአካባቢው ቱሪዝምን ለማሳደግ ያለመ ነው።
አየር መንገዱ የቁጥጥር፣ የደኅንነት፣ የጸጥታና የአሠራር ጥራት መስፈርቶችን ካሟላ በኋላ ባለፈው ሳምንት ከአጠቃላይ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአየር ኦፕሬተር ሰርተፊኬት (AOC) ማግኘቱንም አክለዋል። ለምሥራቃዊ ግዛት ነዋሪዎች ይህ ወደ ዋና ዋና የሳውዲ ከተሞች ተጨማሪ ተመጣጣኝ ቀጥታ በረራዎች ማለት ነው።


