የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ (SPA) እንደዘገበው፣ በደቡብ ምዕራብ ሳዑዲ ዓረቢያ በጃዛን ክልል የሚገኘው የሳምታ አውራጃ ተፈጥሮን ከባህላዊና ማኅበራዊ ቅርስ ጋር ያጣመረ ነው። የእርሻ ሜዳዎች፣ ሸለቆዎች፣ መንደሮች፣ የባሕር ዳርቻዎች፣ የቅርስ ስፍራዎችና ባህላዊ ገበያዎች የሚገኙበት ሲሆን፣ የልማት ፕሮጀክቶችና የሕዝብ መገልገያዎች የመዝናኛ አማራጮችን አስፍተዋል።

የጃዛን ክልል ማዘጋጃ ቤት በሳምታ ማዘጋጃ ቤትና በአስ-ሱሃይና አል-ቀፋል ማዕከላት ማዘጋጃ ቤቶች በኩል በድምሩ 1 ቢሊዮን 628 ሚሊዮን ሪያል የሚገመቱ 156 የተጠናቀቁና በሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ አድርጓል። ዓላማውም መሠረተ ልማትንና የማዘጋጃ ቤት መገልገያዎችን ማልማት፣ የከተማ ገጽታን ማሻሻልና የአገልግሎት ጥራትን ማሳደግ ነው።

ከእነዚህ ውስጥ 822 ሚሊዮን ሪያል የሚገመቱ 89 ፕሮጀክቶች የተጠናቀቁ ሲሆን፣ 806 ሚሊዮን ሪያል የሚገመቱ 67 ፕሮጀክቶች በሂደት ላይ ናቸው። ፕሮጀክቶቹ የመንገድ ግንባታና አስፋልት፣ የእግረኛ መንገድና የመንገድ መብራት፣ የዝናብና የጎርፍ ውሃ ማስወገጃ እንዲሁም የአትክልት ስፍራዎች፣ መናፈሻዎችና የማዘጋጃ ቤት መገልገያዎች ልማትን ያካትታሉ።

የጃዛን ክልል ከንቲባ ኢንጂነር የሕያ አል-ገዝዋኒ በሳምታ፣ በአስ-ሱሃይና በአል-ቀፋል ባደረጉት የመስክ ጉብኝት በርካታ ፕሮጀክቶችን ተመልክተው የሥራ ሂደቱን ገምግመዋል፤ ሥራዎችን ለማፋጠን በሚቻልባቸው መንገዶች ላይም ተወያይተዋል።

እንደ ማዘጋጃ ቤቱ ገለጻ ፕሮጀክቶቹ ሳምታ ጎብኚዎችንና ተዝናኞችን ለመቀበል ያላትን ዝግጁነት ያሳድጋሉ። በጃዛን ክልል ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም አዳዲስ የመዝናኛ አማራጮችን ይፈጥራሉ።