የሳዑዲ አረቢያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዘንድሮው የ1447 ዓ.ሂ. ሐጅ ወቅት መመሪያዎችንና ምክሮችን የያዘ መጽሐፍ አውጥቷል። ሚኒስቴሩ እንዳለው ዓላማው የሐጃጆችን ደኅንነትና ጸጥታ መጠበቅና ሥርዓቱን በሰላም፣ በቀላሉና በእርጋታ እንዲፈጽሙ ማገዝ ነው።

መመሪያው በመካ ወደሚገኘው ታላቁ መስጊድ (አል-መስጂድ አል-ሐራም) እንዴት መድረስ እንደሚቻል የሚያስረዳ ሲሆን ወደ ጠዋፍና ሰዕይ ቦታዎች ለመድረስ የተዘጋጁ የእግረኛ መንገዶችንና መተላለፊያዎችንም ያሳያል።

በተጨማሪም በታላቁ መስጊድና በአደባባዮቹ ከፍተኛ መጨናነቅ የሚኖርባቸውን ሰዓቶች፣ ሐጃጆችን ለማጓጓዝ ተሽከርካሪዎችን ስለመጠቀም የሚሰጡ መመሪያዎችንና የእግረኞችንና የሕዝብ ብዛትን አስተዳደር ደንቦች ይዟል። ሐጃጆች በሁሉም የሐጅ ደረጃዎች ለጠዋፍ፣ ለሰዕይና ለጀመራት ውርወራ የተወሰኑትን ሰዓቶች እንዲያከብሩ ይጠየቃሉ።

መመሪያው «ያለ ፈቃድ ሐጅ የለም» የሚለውን ደንብና ደንቡን በሚጥሱ ላይ የሚጣሉትን ቅጣቶች ያብራራል።

ሚኒስቴሩ ሁሉም ሰው የሐጅ ሕጎችን እንዲያከብርና ጥሰቶችን በመካ፣ በመዲና፣ በሪያድና በምሥራቃዊ ክልል በ911፣ በሌሎች ክልሎች ደግሞ በ999 እንዲያሳውቅ ጥሪ አቅርቧል። መመሪያውን በዚህ ማስፈንጠሪያ ማግኘት ይቻላል፦ https://moi.gov.sa/SharePointMedia/api/Home/GetMediaByURL?ws=&lid=HomeDocs&iid=c69da79f-8620-4c4e-9b3a-f109521166ca

ወደ ሐጅ ለሚሄዱ ሰዎችና ለቤተሰቦቻቸው ከጉዞ በፊት ይህን መመሪያ ማንበብ ጠቃሚ ነው።