የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ (SPA) እንደዘገበው፣ የሳዑዲ አረቢያ የሰው ሀብትና ማኅበራዊ ልማት ሚኒስቴር በግል ዘርፍ በግዢ ነክ ሙያዎች የሳዑዲ ዜጎችን ድርሻ ወደ 70% ከፍ የማድረግ ውሳኔ ከእሑድ ሜይ 31 ቀን 2026 (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ ተግባራዊ መሆኑን አስታውቋል።
ውሳኔው በታለሙት ሙያዎች 3 እና ከዚያ በላይ ሠራተኞች ባሏቸው ተቋማት ላይ የሚመለከት ሲሆን የሙያዎቹ ትርጉምና መጠሪያ በሳዑዲ የተዋሐደ የሙያዎች ምደባ መሠረት ይወሰናል።
ውሳኔው 12 ሙያዎችን ያካትታል፦ የግዢ ሥራ አስኪያጅ፣ የግዢ ተወካይ፣ የኮንትራት ሥራ አስኪያጅ፣ የመጋዘን ኃላፊ (ስቶር ኪፐር)፣ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ፣ የመጋዘን ሥራ አስኪያጅ፣ የጨረታ ባለሙያ፣ የግዢ ባለሙያ፣ የኢ-ኮሜርስ ባለሙያ፣ የገበያ ጥናት ባለሙያ፣ የመጋዘን ባለሙያ እና ለግል ብራንዶች የአቅርቦት ባለሙያ።
የሚኒስቴሩ የቁጥጥር ቡድኖች በታለሙት ተቋማት የውሳኔውን አፈጻጸም መከታተል ጀምረዋል። ሚኒስቴሩ የተሰጠው የጊዜ ገደብ ካበቃ በኋላ ውሳኔውን የማያከብሩ ተቋማት ላይ ሕጋዊ ቅጣቶች እንደሚጣሉ አስገንዝቧል።
እንደ ሚኒስቴሩ ገለጻ፣ ውሳኔው በሥራ ገበያ ስትራቴጂ መሠረት ለብሔራዊ ባለሙያዎች የሥራ ዕድል ለማሳደግ የሚደረገው ቀጣይ ጥረት አካል ነው። በእነዚህ የሥራ መደቦች ላይ ለሚሠሩ ኢትዮጵያውያንና ለቀጣሪዎቻቸው ውሳኔው በቀጥታ የሚመለከታቸው ነው።
