የሳዑዲ ዓረቢያ የባህል ሚኒስትርና የፋሽን ኮሚሽን የቦርድ ሊቀመንበር ልዑል በድር ቢን አብዱላህ ቢን ፈርሐን አል ሳዑድ በሪያድ በሚገኘው ኢስቲቱቶ ማራንጎኒ ተቋም በፋሽን ዘርፍ የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች መጀመራቸውን አስታውቀዋል። የሳዑዲ የዜና ወኪል (ኤስፒኤ) እንደዘገበው ዓላማው የሳዑዲ ተሰጥኦዎችን ከዓለም አቀፍ ልምድ ጋር ማገናኘትና በዓለም የፋሽን ኢንዱስትሪ ያላቸውን ዕድል ማስፋት ነው።

ሚኒስትሩ “በሪያድ በሚገኘው የማራንጎኒ ተቋም የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች መጀመር ልዩ የአካዳሚክ ትምህርትን ለማጠናከርና ከባህል ዘርፉ ፍላጎቶችና እያደጉ ካሉ ዕድሎች ጋር ለማስተሳሰር ትልቅ እርምጃ ነው” ብለዋል።

ማመልከቻ ከኦክቶበር 8 ጀምሮ እስከ ኖቬምበር 4 ቀን 2026 ድረስ የሚቀበል ሲሆን ትምህርቱ በጃንዋሪ 2027 ይጀመራል። የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራሙ የፋሽን ዲዛይንና አክሰሰሪዎች፣ የፋሽን ኮሙኒኬሽንና ምስል እንዲሁም የፋሽን ማኔጅመንትና ዲጂታል ኮሙኒኬሽን የትምህርት መስኮችን ያካትታል፤ በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ ደግሞ በፋሽንና ቅንጡ ብራንድ ማኔጅመንት ዲግሪ ይሰጣል።

አመልካቾች በተቋሙ ድረ ገጽ በኩል ማመልከት ይችላሉ። ከባህል የትምህርት ዕድል ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ ሳዑዲ ተማሪዎች በscholarship.moc.gov.sa መድረክ ላይ ለብቻው ማመልከት ያለባቸው ሲሆን ሁለቱንም ማመልከቻዎች በተወሰነው ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል።

የፋሽን ኮሚሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቡራክ ቻክማክ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የፋሽን ሥርዓት ለመገንባት በሁሉም ደረጃ በተሰጥኦዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የማራንጎኒ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ስቴፋኒያ ቫለንቲ ዕድሉ ለተቋሙ ትልቅ ክብር መሆኑን ገልጸው፣ የሪያድ ተማሪዎች ያንኑ የአካዳሚክ ብቃት፣ በዓለም ዕውቅና ያለው ዲግሪና ከዘጠና ዓመታት በላይ የተገነባ ዓለም አቀፍ ትስስር እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

እነዚህ ፕሮግራሞች ተቋሙ በ2025 በሪያድ ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ ሲሰጡ የቆዩ የዲፕሎማና የሙያ ኮርሶች ማስፋፊያ ሲሆኑ በ2024 በፋሽን ኮሚሽኑና በማራንጎኒ መካከል በተፈረመው የአጋርነት ስምምነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ውጥኑ የብሔራዊ የባህል ስትራቴጂና የሳዑዲ ራዕይ 2030 አካል ነው።