የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ (SPA) እንደዘገበው፣ የሕዝብ ጤና ባለሥልጣን “ወቃያ” ከሳዑዲ ዓረቢያ ውጭ የሚጓዙ ሰዎች በጉዞ ወቅት የጤናና የመከላከያ መመሪያዎችን ቸል እንዳይሉ አስጠንቅቋል። በተለይ ጉዞ በሚጨምርበት የበጋ ወቅት በአንዳንድ አገሮች ለተላላፊ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድል ሊጨምር እንደሚችል ገልጿል።
ባለሥልጣኑ ከዓለም አቀፍ የጤና ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የዓለምን የወረርሽኝ ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን አስታውቋል፤ ከእነዚህም መካከል ሀንታ ቫይረስ፣ የኢቦላ ቫይረስ በሽታ፣ ቢጫ ወባ (የሎው ፊቨር) እና ወቅታዊ ጉንፋን ይገኙበታል። እንደ ባለሥልጣኑ ገለጻ፣ ሀንታ ቫይረስ በአብዛኛው በተበከሉ አይጦች ፈሳሽ፣ ኢቦላ በበሽተኛ ሰው ወይም እንስሳ ደምና የሰውነት ፈሳሽ ቀጥተኛ ንክኪ፣ ቢጫ ወባ በትንኝ ንክሻ፣ ጉንፋን ደግሞ በትንፋሽ ጠብታዎች ይተላለፋሉ።
“ወቃያ” መንገደኞች ከመነሳታቸው በፊት የመድረሻ አገራቸውን የጤና ሁኔታና የክትባት መስፈርቶች እንዲያጣሩ፣ በተለይም የምስክር ወረቀት በሚጠየቅባቸው አካባቢዎች የቢጫ ወባ ክትባት እንዲወስዱ መክሯል። ከታመሙ ሰዎች፣ ከዱር እንስሳትና ከአይጦች መራቅ፣ እጅን አዘውትሮ መታጠብ፣ የምግብና የውኃ ደኅንነትን መጠበቅ፣ የትንኝ መከላከያ መጠቀምና በጉዞ ወቅት ተገቢ የጤና መድን መያዝም ተመክሯል።
ባለሥልጣኑ በጉዞ ወቅት ወይም ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ከተመለሱ በኋላ የሕመም ምልክቶች ከታዩ በአቅራቢያ ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ ለሐኪሙ የጉዞ ታሪክን ማሳወቅ እንደሚገባ አሳስቧል። በበጋ ዕረፍት ወደ አገር ቤት ወይም ወደ ሌሎች አገሮች ለሚጓዙ ነዋሪ ቤተሰቦች ይህ ምክር በተለይ ጠቃሚ ነው። ባለሥልጣኑ ወሬዎችን ከማሰራጨት እንዲቆጠቡና በድረ ገጹ የሚወጡ የጉዞ ማሳሰቢያዎችን እንዲከታተሉም ጥሪ አቅርቧል።
