የሳዑዲ የዜና አገልግሎት እንደዘገበው፣ የሳዑዲ አየር መንገድ (ሳዑዲያ) እና ጋሩዳ ኢንዶኔዥያ ስትራቴጂያዊ አጋርነታቸውን ወደ አዲስ የመቀናጀት ምዕራፍ የሚያሸጋግር የጋራ የንግድ ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በኢንዶኔዥያ የሳዑዲ አምባሳደር ፈይሰል ቢን አብዱላህ አል-ዓሙዲ በተገኙበት የሳዑዲያ ግሩፕ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ኢብራሂም አል-ዑመር እና የጋሩዳ ኢንዶኔዥያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ግሌኒ ካይሩፓን ስምምነቱን ፈርመዋል።
ስምምነቱ በሐምሌ 2026 ይፋ የተደረገው የመግባቢያ ሰነድ ቀጣይ ነው። አሁን ሁለቱ አየር መንገዶች በ2027 የጋራ ንግዱን ለመጀመር የቁጥጥር ፈቃዶችን የማግኘት ሂደት ይጀምራሉ።
ይህም ኢንዶኔዥያንና አውስትራሊያን ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከአውሮፓና ከአፍሪካ ጋር የሚያገናኙ የጉዞ አማራጮችን ያሰፋል። ሁለቱ መረቦች በጋራ ከ120 በላይ መዳረሻዎችን ይሸፍናሉ። አጋርነቱ የተቀናጁ የዋጋ አማራጮችንና በታማኝነት ፕሮግራሞች፣ በቴክኖሎጂና በአውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎቶች ትብብርን ያካትታል።
ከኢንዶኔዥያ ለሚደረጉ የሐጅና የዑምራ ጉዞዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል። ኢብራሂም አል-ዑመር ዓላማው መረቡን ማስፋት ብቻ ሳይሆን ለተጓዦች ምቹ ልምድ መስጠትና ከኢንዶኔዥያ የሚመጡ ሐጃጆችንና ዑምራ አድራጊዎችን ጉዞ ማሻሻል መሆኑን ተናግረዋል።
