የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ (SPA) እንደዘገበው፣ የሲቪል አቪዬሽን ጠቅላላ ባለሥልጣን (GACA) ለአሜሪካው ዴልታ አየር መንገድ (Delta Air Lines) በአቪዬሽን ደኅንነት አስፈጻሚ ደንብ ክፍል 129 መሠረት የውጭ አየር ኦፕሬተር ፈቃድ ሰጥቷል። ይህም ኩባንያው በአትላንታና በሪያድ መካከል መደበኛ ቀጥታ በረራዎችን እንዲጀምር መንገድ ይከፍታል።
የGACA የአቪዬሽን ደኅንነትና የአካባቢ ዘላቂነት ዋና ምክትል ፕሬዚዳንት ካፒቴን ሱለይማን ቢን ሷሊሕ አል-ሙሐይሚዲ ፈቃዱን በሪያድ በሚገኘው የባለሥልጣኑ ዋና መሥሪያ ቤት ለዴልታ አየር መንገድ ተወካይ አስረክበዋል።
ባለሥልጣኑ እንዳስታወቀው ፈቃዱ የመንግሥቱን ዓለም አቀፍ የአየር ትስስር ለማጠናከርና ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች ወደ ሳዑዲ ገበያ እንዲገቡ ለማስቻል የሚደረገው ጥረት አካል ነው።
ዓላማውም የአቪዬሽን ዘርፉን ተወዳዳሪነት ማሳደግ፣ የመንግሥቱን የአየር ትስስር መረብ ከዓለም አቀፍ ገበያዎችና መዳረሻዎች ጋር ማስፋትና የቱሪዝም፣ የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን መደገፍ ሲሆን፣ ይህም ከአቪዬሽን ፕሮግራምና ከሳዑዲ ራዕይ 2030 ግቦች ጋር የሚጣጣም ነው።
