የሳዑዲ ዓረቢያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጠው የመግቢያ ቪዛ ጊዜ ካበቃ በኋላ ከአገር ለመውጣት የሚዘገይ የውጭ ዜጋ እስከ 50,000 ሪያል የገንዘብ ቅጣት፣ እስከ 6 ወር እስራትና ከአገር መባረር እንደሚጠብቀው አጽንኦት ሰጥቶ ገልጿል።

የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ (SPA) እንደዘገበው፣ ሚኒስቴሩ ይህን ማስጠንቀቂያ ያወጣው ከዘንድሮው (1447 ሂጅራ) የሐጅ ወቅት ጋር በተያያዘ ነው። ሁሉም ሰው የሐጅ ወቅት መመሪያዎችን እንዲያከብርና ለሐጃጆች ደህንነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንዲተባበር ጠይቋል፤ መመሪያዎቹን የሚጥሱ ሕጋዊ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

ሚኒስቴሩ ጥሰቶችን በመካ፣ በመዲና፣ በሪያድና በምሥራቃዊ ግዛት በ911፣ በሌሎች የመንግሥቱ አካባቢዎች ደግሞ በ999 እንዲጠቁሙ ጥሪ አቅርቧል።

በጉብኝት ወይም በሌላ ጊዜያዊ ቪዛ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ለመጡ ኢትዮጵያውያንና ለሚያስተናግዷቸው ቤተሰቦች፣ የቪዛው ጊዜ ከማብቃቱ በፊት ከአገር መውጣት አስፈላጊ መሆኑን የሚያስታውስ መልዕክት ነው።