የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ (SPA) እንደዘገበው፣ የበጎ ፈቃድ የጥርስ ሕክምና አገልግሎቶች ማኅበር “ኢብተሲም” ለአላህ እንግዶች የሕክምናና የግንዛቤ ማስጨበጫ አገልግሎቶችን መስጠቱን ቀጥሏል። ማኅበሩ በመካ በሚገኙ ቋሚ ክሊኒኮቹ በየቀኑ ከ100 በላይ የዑምራ ተጓዦችንና ጎብኚዎችን የሚቀበል ሲሆን፣ ዓላማውም ታላቁን መስጊድ ለሚጎበኙ ሰዎች ነፃ የአፍና የጥርስ ጤና እንክብካቤ ማቅረብ ነው።

አገልግሎቶቹን 42 ሐኪሞችንና ወንድና ሴት በጎ ፈቃደኞችን ያካተተ ቡድን የሚሰጥ ሲሆን፣ ቡድኑ የሕክምና፣ የመከላከልና የጤና ትምህርት አገልግሎቶችን ያቀፈ የተሟላ ፓኬጅ በማቅረብ ተጓዦች በመካ በሚቆዩበት ጊዜ ፍላጎታቸው እንዲሟላ ያደርጋል።

በመካ ክልል የማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብዱልአዚዝ ፈትኒ ማኅበሩ የሰው ኃይሉንና የሕክምና አቅሙን የአላህ እንግዶችን ለማገልገል ማዋሉን ገልጸዋል። ለምርመራ፣ ለሕክምናና ስለ ጥርስ ጤና ግንዛቤ ለማግኘት ወደ ቋሚ ክሊኒኮቹ የሚመጡ ሰዎች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደ ፈትኒ ገለጻ፣ ማኅበሩ ለሚቀበለው ለእያንዳንዱ ተገልጋይ ከሁለት እስከ ሦስት አገልግሎቶች የሚሰጥ ሲሆን፣ ይህም በወር በሺዎች የሚቆጠሩ አገልግሎቶች ማለት ነው። ከኢትዮጵያና ከሌሎች አገሮች ለሚመጡ የዑምራ ተጓዦች በጉዞ ወቅት የጥርስ ሕመም ቢገጥማቸው በመካ ይህ ነፃ አገልግሎት መኖሩን ማወቅ ጠቃሚ ነው።