የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ (SPA) እንደዘገበው፣ ሳዑዲ አረቢያ በውጭ ንግድ ጠቅላይ ባለሥልጣን በኩል ሐሙስ ዕለት ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በበይነ መረብ የቴክኒክ ስብሰባ አካሂዳለች። ስብሰባውን የባለሥልጣኑ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክትል ገዥ ዐብዱልዐዚዝ ቢን ዑመር አል-ሰክራንና የአውሮፓ ኮሚሽን የንግድ ዋና ዳይሬክቶሬት የመካከለኛው ምሥራቅ ግንኙነት ኃላፊ ኢግናሲዮ ዲዬዝ በጋራ መርተዋል።
በስብሰባው የሳዑዲ የደረጃዎች፣ የሥነ-ልክና የጥራት ድርጅት የተስማሚነትና የኦፕሬሽን ምክትል ገዥ ኢንጂነር ዐብዱልመጂድ አል-ውሀይቢ፣ የሳዑዲ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሥራ አስፈጻሚ ጉዳዮች ረዳት አላእ ሲንዲ እና በአውሮፓ ኅብረት የሳዑዲ ሚሲዮን የኢኮኖሚ ክፍል ኃላፊ ኻሊድ አል-ዐነዚ ተሳትፈዋል።
ስብሰባው በሳዑዲ አረቢያና በአውሮፓ ኅብረት መካከል ባሉ ዋና ዋና የንግድና የቴክኒክ ተግዳሮቶችና እንቅፋቶች እንዲሁም ምርቶች ወደ ሁለቱም ወገኖች ገበያ በቀላሉ እንዲገቡ የሚያግዙ መፍትሔዎችን በማፈላለግ ላይ ተወያይቷል።
እንደ ኤጀንሲው ገለጻ ሳዑዲ አረቢያ በቀጣናው የአውሮፓ ኅብረት ቀዳሚ የንግድ አጋር ስትሆን፣ በ2025 በሁለቱ ወገኖች መካከል የነበረው የንግድ ልውውጥ 84.2 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ደርሷል።
